በመትከል ማንሰራራት! የጤና ቢሮ የዘርፉ የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ችግኝ የመትከል መርሃ ግብር አካሄዱ። ሐምሌ 6/2017 ዓ.ም (አቃቂ ቃሊቲ) በ7ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ ንቅናቄ የጤና ቢሮ፣ የዘርፉ የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሂደዋል ። በመርሃ ግብሩ የጤና ቢሮ ኃላፊዎች፣ ሰራተኞች፣ የ11ም ክፍለ ከተሞች ጤና ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች፣ የጡሩነሽ ቤጂንግ ጠቅላላ ሆስፒታል እና ሌሎች በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተሮች፣ የጤና ጣቢያ የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች የወረዳ 2 አመራሮች እና የወረዳው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል። ከ1ሺ500 በላይ የተለያየ አይነት የጥላ እና የውበት ችግኝ የተተከለ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ሙሉጌታ እንዳለ በመርሃ ግብሩ የሰው ልጅ ህይወት ህልውና ከደን እና ዛፍ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ የአረንጓዴ እና ለአከባቢ ጥበቃ ስራ ሁሉም በትኩረት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አዕምሮ ጥላሁን እጽዋት ለመድኃኒትነት ግብአት የሚሆኑ በመሆኑና ከጤና ዘርፍ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ዛሬ የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራውም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። የጤና ባለሙያው የሰው ህይወትን ከማዳን ባሻገር በሌሎች ማህበራዊ ኃላፊነት እና በአከባቢ ጥበቃ ስራ እያሳየ ያለው ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገልጿል።